ወያኔ በሕዝብ ላይ የሚፈጽመውን ግፍና ግድያ እናውግዝ

By | 24th December 2015

ታህሳስ 13 ቀን 2008: ጨቋኙ የወያኔ አገዛዝ በቅርቡ ተቀስቅሶ ያለውን የሕዝብ ተቃውሞ ለማፈን ሲጥር በርካታ ንጹህ ዜጎችን መግደሉ በይፋ ተነግሯል። ጸረ ሰላም ሀይሎች በሚል በተለመደው ሽፋኑ ተቃዋሚዎችን ከሶ ግድያቸውንም ማጠየቂያ ሊሰጥ መሞከሩንም ዜጎች ሁሉ የታዘቡት ነው። በርካታ ዜጎችንም ታግተው ስየል እየተቀበሉ ናቸው። ይህን ሁሉ ግፍና ግድያ ኢፖእአኮ አጥብቆ ያወግዛል።

ከአምቦ እስከ ሀሮማያ፤ ከጅማ እስከ ጎንደር፤ ጋምቤላ፤ ዋልድባ፤ ኦጋዴን፤ ወዘተ ዜጎች የወያኔ የግፍ በትር እየመታቸው ነው። የአዲስ አበባ መስፋፋት ወይም ማስተር ፕላን ብሎ አገዛዙ ያመጣውን ዕቅድ ተቃውሞ ያሰሙ ዜጎች ሲጠቁ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ገዢው ክፍል የሕዝብ መሬት እየነጠቀና ለባዕድ እየሰጠ ወይም እየሸጠ በዚያውም ሺዎችን እያፈናቀለ የቆየ ነው። የግዳጅ ሰፈራም ከተጀመረ ዓመታት አልፈዋል። አገዛዙ ሰፊ የመብት ረገጣ ሲያደርግ ከሃያ አመታት በላይ ሆኖታል። በሀይማኖት ጉዳይም ጣልቃ እየገባ ምዕመናን እየጎዳ ነው — አደባባይ ኢየሱስ፤ አንዋር መስጊድ፤ ለእስር የተዳረጉና የተገደሉ የሀይማኖት መሪዎችና ተከታዮች ምስክር ናቸው። በቃሊቲ፤ ቂሊንጦ፤ ዝዋይ፤ ወዘተ ስንቱ የፖለቲካ እስረኛ መከራ እያየ ነው። ስየል የተለመደና የተስፋፋ ነው፤ ፍትህ ደብዛዋ ከጠፋ ዓመታት አልፈዋል፤ ፍትሃዊ አተዳደር የህልም እንጀራ እንደሆነ አለ። በዚህ በዚያ ተቃውሞ በተከሰተበት ሁሉ አገዛዙ ግድያና አፈና እያካሄደ ነው ያለው። ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ በዚሁ ሰበብ ደግሞ የጥላቻ በሽታቸውን ለማከም ንጹህ ህዝብን የተወሰነ ብሄረሰብ አባል በሚል ግድያ የሚፈጽሙትንም ቢሆን ኢፖእአኮ ያወግዛል።

አገዛዙ በሰፊው የህዝብን መብት ረገጣውን እንዲያቆም መደረግ አለበት። ይህን እውን ለማድረግ ዜጎች ተባብረው ሊታገሉ ይጠበቃል። ለሰብዓዊ መብት ቆመናል የሚሉ ብዙዎች የአንገት በላይ ነው መቆሮቆራቸው እንደታየው ከሆነ። ሕዝብ ሲበደልና ሲረገጥ ማመጽ ግዴታው መሆኑ ደግሞ ክርክርን አይጠይቅም — ሰብዓዊ መብት በስጦታ አይገኝምና። ብዙዎች ባለፉት ሳምንታት ተገድለዋል ፤ ወጣቶች ተቀጥፈዋል፡፡ ይህን ኢፖእአኮ ያወግዛል ። የሕዝቡንም ትግል ይደግፋል። ካልታገሉ መብት አይከበርምና። በሕዝብ መሃል ጥላቻ የሚያሰራጩትንም ኮሚቴው መቃውሙና ማጋለጡ ግዴታው ነው። መሬት ንጥቂያ ያክትም፤ ሕዝብን ማፈናቀል ይቁም፤ የግድ ሰፈራ ይወገድ፤ በአጠቃላይም የመብት ረገጣው ቆሞ ሁሉም የፖለቲካና የፍትህ መጓደል እስረኞች ይፈቱ። ይህ ነው የህዝብ ጥያቄ፤ መስተጋባት መከርም ያለበት ጥያቄ። የወያኔ ወዳጆች ሆነው በዕብሪቱና ግፉ ወደዱም ጠሉም ተባባሪ የሆኑትንም ደጋፊዎቹንም ጥብቅ ማሳሳቢያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ይገኛል።

የህዝብ ህብረት ይጠንክር!!
በሕዝብ ላይ ግፍና ግድያው ይቁም!
መብት ረገጣው ያብቃ!!pdf_print
ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *